የመከላከያ ስፖርት ክለብ በጦር ሀይሎች ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚገኙ የጦር ጉዳተኞች ድጋፍ አደረገ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የመከላከያ ስፖርት ክለብ በጦር ኀይሎች ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሚገኙ እና በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ዜጎች ከ190 ሺሕ ብር በላይ ግምት ያለዉ የአልባሳትና የንጽህና መስጫ እቃዎች  ድጋፍ አደረጉ፡፡

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ብርጋዴር ጄነራል አስፋው  የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆናችሁና ሀገራችንን ለመታደግ የአካልና የህይወት መስዋዕትነት የከፈላችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ መቼም የማይረሳ ታሪክ ሰርታችኋል ብለዋል።

ጄኔራል መኮንኑ ድጋፉን ያደረግነዉ ያለንን ወንድማዊነት ለማሳየት ነው ያሉ ሲሆን፣ በዳይሬክተሩ የሚገኙ የተለያዩ ክፍሎችም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የሆስፒታሉ አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ዶክተር ሀይሉ እንዳሻው በበኩላቸዉ፣ የሰራዊቱ አካል የሆነው የመከላከያ ስፖርት ክለብ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዉ፣ ድጋፉ በተገቢው ሁኔታ ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ማረጋገጣቸዉን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል።