ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – የ2013/14 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የኬሚካልና የግብርና ኖራ ግብዓቶች በስፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ በዘንድሮው ምርት ዘመን የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት ከ2012 ሐምሌና ነሐሴ ወራት ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የኬሚካልና የግብርና ኖራ ግብዓቶች ግዢ 1 መቶ በመቶ ተፈጽሞ በስፋት ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በምርት ዘመኑ በአርሶ አደሩ ፍላጎት መሰረት ለማቅረብ ከታቀደው 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል አራት ዓይነት የአፈር ማዳበሪያ ከዩሪያ ውጪ ያለው 15 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ወይም 85 በመቶው ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሱንና ከደረሰውም 14 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታሉን ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማጓጓዙን አስታውቀዋል።
አፈጻጸሙ የዓመታዊ ዕቅዱ 85 በመቶ፤ ጅቡቲ ወደብ የደረሰውን በማጓጓዝ በኩል ደግሞ 94 በመቶ ያሳካ ነው ያሉት አቶ መንግስቱ፣ 17 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በመጋዘን የነበሩ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው የአፈር ማዳበሪያ መኖራቸውን አመልክተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።