የመገናኛ ብዙኃን አቅምን ለማሳደግ በዘርፉ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ሊበራከቱ ይገባል ተባለ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙኃን አቅምን ለማሳደግ እና በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዘርፉ የሚደረጉ የጥናትና የምርምር ስራዎች ሊበራከቱ እና ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ትስስርን ማጎልበት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ በመካሔድ ላይ ነው።
በኢትዮጵያ ናሽናል ሳፖርት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙኃን አውድ ለመደገፍ የሚረዱ አቀራረቦች እና ስልቶች ሊጎለብቱ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚመክር የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ስራ አስኪያጅ ሰብስቤ ከበደ ገልፀዋል።
የምክክር መድረኩ የመገናኛ ብዙኃን ሙያና ልህቀትን ለማጎልበት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን ምህዳር በአግባቡ ለማስፋት የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የአመራር አባል ታምራት ኃይሉ ናቸው።
የመገናኛ ብዙኃንን ስነምግባር በአግባቡ ሳይገነዘቡ ሙያውን እያዛቡ ያሉ ተግባራትን ለማስወገድ እንዲህ አይነት የጋራ መድረክ መፈጠሩ ጠቃሚ ነው ሲሉም አክለዋል።
በቀጣይም ዘርፋን ለማሳደግ የጥናት እና ምርምር ስራዎችን በጥራት እና በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም በመድረኩ የተነሳ ሲሆን በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የመገናኛ ብዙኃንን ትስስር ማሳደግ እንደሚገባ ተመልክቷል።
በድልአብ ለማ