የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሐኒቶች ደብቆ ወደ መሀል ሀገር ሊያስገባ የነበረ አሽከርካሪ ተያዘ

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) የማረጋገጫ ፈቃድ የሌላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሐኒቶች በሲሚንቶ ጭነት ስር ደብቆ ወደ መሀል ሀገር ለማስገባት የሞከረ አሽከርካሪ ትናንት ምሽት 5፡00 ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የጭሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ካሳሁን ባይሳ እንደገለጹት፤ አሽከርካሪው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 – 80691 አ.አ በሆነ ኤፍኤስአር የጭነት ተሽከርካሪ መድሐኒቱን በመደበቅ ከሀረር ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እንዳለ በጭሮ ኬላ በተካሄደ ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ለራስ ምታትና ጀርባ ህመም እንዲወሰዱ የተዘጋጁ፣ የማረጋገጫ ፈቃድ የሌላቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሐኒቶች በፍተሻው መያዛቸውን ገልጸዋል ሲል የዠገበው ኢዜአ ነው።

የተያዙት አምስት ቦንዳ መድሀኒቶች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን ዋና ሳጅን ካሳሁን አስታውቀዋል።