የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን የማምረት አቅም ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን የማምረት አቅም ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢ/ር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

በገበያ ላይ ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ለመቅረፍ የሙገር ሲሚንቶን አቅም ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሩ ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ኮርፓሬሽን የቦርድ አባላት ጋር በጋራ በመሆን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን እንዲጠቀምና የሲሚንቶ አቅርቦቱ እንዲጨምር ብሎም የገበያ ትስስሩ እንዲያድግ እንደሚሠራ በፋብሪካው ባደረጉት ጉብኝት ወቅት አብራርተዋል።

ፋብሪካው ያለበት ቦታ ለሲሚንቶ ግብዓት መሆን የሚችል የተፈጥሮ ሀብት በብዛት የሚገኝበት ቢሆንም ፋብሪካው የሚያመርተው ምርት ዝቅተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ከጉብኝቱ በኋላ ገልጸዋል።

በዚህም የፋብሪካውን ምርትና ተደራሽነት በማስፋት ይህ የገበያ ድርሻ ከፍ እንዲል ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ፋብሪካው ምርቱን በዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርብ ቢሆንም ገበያ ላይ በእጥፍ እየተሸጠ እንደሆና የማስተካከል ሥራ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል።