የሚሰሩ የምርምር እና ፈጠራ ስራዎች በእውቀት ላይ የተመሰረቱ መሆን ይገባቸዋል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ መምህራን፣ ሠራተኞች እና ተማሪዎች ጋር በትምህርት ጥራት ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የኅልውና ጦርነት የትምህርት ጥራትና የሞራል ውድቀት የፈጠረው ችግር መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት የትምህርት ጥራት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በሁሉም መስክ አዳዲስ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎችን በመስራት እንደትውልድ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ከፍለን ሀገሪቱን ከድህነት ማውጣት አለብን ያሉት ሚኒስትሩ የምንሰራው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች በእውቀት ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በቀጣይ የመምህራንና ሰራተኞች ብቃት ለማሳደግ፣ ትምህርትን ከፖለቲካ መለየት እና ዩኒቨርሲቲዎችን ከአካባቢያዊነት ችግር ለማላቀቅ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል የምርምር ጥራት ችግርች መፈታት አሉባቸው ያላቸውን ጥያቄዎች አቅርበው ውይይት አካሂደዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ ሚኒስትር ዴኤታ  ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ሚኒስትር አመራሮች የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎችን መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡