የሚኒስትሮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ እንዲያደርገው የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

                                                      የሚኒስትሮች ምክር ቤት

ጥር 18/2014 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የሃገር ኅልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ በሚመለከት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ሕወሓት እና ግብረአበሮቹ በሃገራችን ኅልውና እና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀኑ በመሆኑ እና ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ማወጁ ይታወሳል።

አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ፀድቆ በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 አንቀጽ 11(2) በተደነገገው መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ከተቀየሩ እና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ ካመነ የስድስት ወር ጊዜው ሳይጠናቀቅ ጊዜውን የማሳጠር ስልጣን ያለው በመሆኑ የአዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ እንዲያደርገው የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጥልቀት ተወያይቶ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡