መስከረም 21/2017 (አዲስ ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 39ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
በ39ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የመካከለኛ ዘመን 2017-2020 የገቢ ስትራቴጂ ላይ ነው፡፡ ስትራቴጂው የታክስ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለግል ኢንቨስትመንቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የታለመ ሲሆን አጠቃላይ የታክስ ፖሊሲዎችን እና አስተዳደራዊ ሪፎርሞችን እንዲሁም ማሻሻያዎችን ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡ ሰትራቴጂው ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ተደርጎ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በስትራቴጂው ላይ በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ በምክር ቤቱ ውሳኔ ካገኘበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ከማልታ ሪፐብሊክ መንግስት እና ከቻድ ሪፐብሊክ መንግስት ጋር የተፈረማቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ 2 ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡ ስምምነቶቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማንኛውም የማልታ ከተማ እና ወደ እንጃሜና ከተማ በ3ኛና 4ኛ ትራፊክ መብት የመንገደኛ እና የጭነት የበረራ ምልልስ ለማድረግ፣ ተወካይ አየር መንገዶችን በሽርክና ለማሰራት፣ በ5ኛ ትራፊክ መብት ወደ ተመረጡ መዳረሻዎች በረራ ለማድረግ የሚያስችል እና አገራችን ከሁለቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት፣ ለወጪ ንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ስምምነቶች ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
3. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ኮንቬንሽን ለማጽደቅ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ኮንቬንሽን በአባል አገራት መካከል ሕብረት በመፍጠር የኢንዱስትሪ ንብረትን ለመጠበቅ፣ የፈጠራ ባለቤትነት፣ የግልጋሎት ሞዴሎች፣ የኢንዱስትሪ ንድፎች፣ የንግድ ምልክቶች፣ የአገልግሎት ምልክቶች፣ የንግድ ስሞች፣ የምርቶች ምንጭ አመልካች ምልክቶች ለመጠበቅ እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ ውድድር ለመከላከል እና ለግብርና እና ሁሉንም የተመረቱ ወይም ተፈጥሯዊ ምርቶች የሚያካትት ነው፡፡ የኮንቬንሽኑ መጽደቅ ሀገራችን ለምታደርገው የአለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ድጋፍ የሚሆን ሲሆን ከአባል ሀገራቱ ለሚነሱ የኢንዱስትሪያዊ ንብረት ጥበቃን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ለመስጠት ያስችላል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የዓለም አቀፍ ምልክቶችን ከሚመለከተው የማድሪድ ስምምነት ጋር የተዛመደውን ፕሮቶኮል ለማጽደቅ በወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ፕሮቶኮሉ የንግድ እና የአገልግሎት ምልክቶች በአገር ውስጥ ሕግ ከሚደረግላቸው ጥበቃ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ ምርቶች እና አገልግሎቶች ያላግባብ ለሌሎች ጥቅም እንዳይውሉ በቂ ጥበቃ የሚደረግበትን ሁኔታ የሚፈጥር፣ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችና አገልግሎቶች እንዲኖሩና የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምክር ቤቱ በፕሮቶኮሉ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ደንብ እና የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች ደንብ ላይ ነው፡፡ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ሀላፊነት ለመወጣት፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት እንዲሁም ከፓስፖርት የቆይታ ጊዜ ጋር በተያያዘ ያሉ ጥቄዎችን መፍታት እንዲችል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የጀመረውን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ፣ ሪፎርሙ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ለማስቻል የአገልግሎቱን ልዩ ባህሪይ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በዝርዝር ከተወያየባቸው በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡