የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በእውቀት ላይ የተመሠረተ የግጭት መከላከል ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አገኘሁ ተሻገር

መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአስተባባሪና የማኔጅመንት አባላት የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በእውቀት ላይ የተመሠረተ የግጭት መከላከል ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

በውይይት መድረክ የሚገኙ ግብዓቶችን በማካተት ስትራቴጂውን በቀጣይ የሥራ መመሪያ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።

የስትራቴጂ ሰነዱን ለመድረኩ ያቀረቡት ብዙነህ አሰፋ የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ ስትራቴጂውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተፈጸሙትንና ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ግጭቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍታት ነው ብለዋል።

የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ በኢትዮጵያ ሰላምን በመገንባት፣ ግጭቶችን በመፍታትና የግጭት ምልክቶችን ቀድሞ በመከላከል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴና የጽኽፈት ቤቱ ማኔጅመንት አባላት በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ መክሮ ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጥበታል ተብሎ እንደሚታሰብ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW