የማንነትና የወሰን ጥያቄ ላይ በ58 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጥናት ማድረጉ ተገለፀ

ታኅሣሥ 22/2014 (ዋልታ) የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የማንነትና የወሰን ጥያቄ ከሚነሳባቸው ውስጥ በ58 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥናት ማድረጉን ገለፀ፡፡

ኮሚሽኑ በአስተዳደር ወሰኖች፣ ከማንነትና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ዙሪያ ጥናትና ምርምር እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም ጥናቱን ለማድረግ ካሰበባቸው 68 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በ58 ዞኖች ላይ ጥናት ማድረጉ ተነግሯል።

ኮሚሽኑ በሥራ ሂደቱ ከትግራይ ክልል ውጪ ከሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

አሸባሪውና ወራሪው ትሕነግ ትግራይ ክልል ውስጥ መሽጎ ጦርነት መክፈቱ የሚታወቅ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ጥናትና ምርምር ሲያደርግ ማንነትን የሚመለከት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ አስተዳደር ወሰን እንዲሁም ተያያዥ ሕግና ፖሊሲን የሚመለከቱ ሰነዶች ላይ ትኩረት ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ሰርቶ ለጥፎታል ተብሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጨ የሚገኘው ካርታ ኮሚሽኑ የሰራው ሳይሆን በአገር ላይ ግጭትና ሁከት እንዲነሳ ለማድረግ ያለሙ አካላት የለጠፉት የሴራ መገለጫ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡