የማይካድራው ጭፍጨፋ በሕወሓት መዋቅር ተፈፅሟል – ሪፖርት

                             በማይካድራ አማራ ተወላጆች ላይ ብሔርን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጭፍጨፋ

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) – በማይካድራ አማራ ተወላጆች ላይ ብሔርን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ሳምሪ በተሰኘው የሕወሓት ገዳይ የወጣት ቡድን እና በሕወሓት አመራርና ታጣቂዎች መፈፀሙን ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብረት ጥሰት ጥምር የምርመራ ሪፖርት አረጋገጠ፡፡

ጥቅምት 24 ሌሊት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመክፈት ጦርነት የከፈተው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከጥቅምት 27 እስከ 30/2013 በማይካድራ የሚኖሩ አማራዎችን በመለየት የዘር ጭፍጨፋ መፈፀሙን የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በጋራ ያደረጉት ምርመራ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡
ዛሬ ይፋ የሆነው ሪፖርቱ ዘርን መሰረት አድርጎ በተፈፀመው ጭፍጨፋ ሳምሪ ከተሰኘው ቡድን በተጨማሪ አካባቢውን ያስተዳድር የነበረው የሕወሓት መዋቅር ውስጥ ያሉ የቀበሌ አመራሮችና ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡
የሽብር ቡድኑ በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ከ1 ሺሕ በላይ ንፁሃንን በግፍ ገድሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን እውነቱ በተደጋጋሚ ሲያሳውቅና ገዳይ ቡድኑም ጭፍጨፋውን ከፈፀመ በኋላ ወደ ሱዳን በመሸሽ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ መግባቱ ሲገለፅ የነበረ ቢሆንም ለሽብር ቡድኑ ያደሩ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ይህን እውነት ደፍረው የዘገቡበት ወቅት አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ወንጀል ራሱን ለማንፃትና መንግሥትን ሲኮንን የነበረውን ሕወሓት ሲደግፉና የወንጀሉን ፈፃሚ ሲያድበሰብሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡