የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል የዝግጅት ሂደት ላይ ውይይት ተካሄደ

ሚያዝያ 26/2014(ዋልታ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደውን የምስራቅ አፍሪካ ሕዝቦች የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል የዝግጅት ሂደትና ቀጣይ መከናወን በሚገባቸው አበይት ተግባት ላይ መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ካደረጉ የኤምባሲ ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም ሁነቱ የሚካሄድበትን ጊዜና ቦታ፣ ፌስቲቫሉ መካሄድ በአገራቱ መካከል ስለሚኖረው ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም የክፍለ አህጉሪቱን የሕዝብ ለሕዝብ የግንኙነት ከማጠናከር አንጻር እና ፖለቲካዊ ውህደትን ከማጎልበት አኳያ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተግባራት ያሉበትን ሂደት እና አጠቃላይ የሁነቱን ዓላማ አስመልክቶ ዝርዝር ገለፃ ያደረጉት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አህመድ መሀመድ ሲሆኑ፤ በቀረቡት ዐበይት የሥራ አፈፃጸምና ቀጣይ መከናወን በሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ እንደመሆኑ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸው ገምግሟል፡፡
ውይይቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና የምስራቅ አፍሪካ አገራትን ትስስር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲያጠናክር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ለአንድ ጊዜ ተካሂዶ መቆም የሌለበት ሁነት በመሆኑ የሀገራቱ የባህል ሚኒስትሮች ሥራውን በዘላቂነት ይዘው በየአመቱ የሚዘጋጅበት ሁኔት ሊፈጠር እንደሚገባ መገለጹን ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።