የምክር ቤቱ አባላት የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላትን ጎበኙ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) የኢዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአራዳ እና ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላትን ጎበኙ።

ማዕከላቱ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በቀን አንድ ጊዜ እንዲመገቡ የሚያደርግ ሲሆን በከተማ ደረጃ የማዕከላቱ ቁጥር ስድስት ደርሷል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ፋይዛ መሀመድ በአድዋ ድል እንዳደረግን ሁሉ ድህነትን ማሸነፍ አለብን፤ በአድዋ አንድ ላይ ተባብረን እንደቆምነው ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችንም ለመርዳት መተባበር አለብን ብለዋል፡፡

በከተማዋ መመገብ የማይችሉ ወገኖች እና በከተማዋ የሚገኙ የምገባ ማዕከላት ቁጥር እንደማይመጣጠኑ በመግለጽ በበጀት በመደገፍም ሆነ በአንድነት በመረባረብ የማዕከላቱን ቁጥር ማሳደግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡

በማዕከላቱ የተቸገሩትን ከመመገብ ባለፈ ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ መፍጠርም እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

በከተማዋ ስድስት የምገባ ማዕከላት ያሉ ሲሆን ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎችን መመገብ ማስቻሉም ተነግሯል።

በጉብኝቱ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ፋይዛ መሀመድ፣ የምክር ቤቱ ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዘይነባ ሽብር እና ሌሎችም የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።

በትዕግስት ዘላለም