የምክር ቤቶች አባላት ለሠራዊቱ ደም ለገሱ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ሀብት በማሠባሰብ፣ ደማችንን በመለገስና በሚያስፈልገው ሁሉ በመደገፍ የሚጠበቅብንን ማከናወን አለብን ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ዘሃራ ኡመድ በበኩላቸው መከላከያ ሰራዊታት በጫካ እየተዋደቀ ያለው የኛን ሰላም ለማስከበር እና ሁላችንም በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ እንድንሆን እንዲሁም በሰላም ወጥተን እንድንገባ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በደም መፍሰስ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳያጡ መደገፍ እና እያበረከቱ ስላሉት አስተዋጽኦ ማመስገን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቶቹ አባላት በበኩላቸው የሀገርን ኅልውና እያስቀጠለ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ደጀንነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

ሀገር ወደ ሙሉ የልማት ጎዳና እስክትመለስ ድረስ ሁሉም ድጋፍ ማድረጉን ሊቀጥል እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በብሩክታይት አፈሩ