የምዕራባውያን አገራት ጫና የሚቃወም ሰልፍ በፕሪቶሪያ እየተካሄደ ነው

ኅዳር 20/2014 (ዋልታ) አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉትን ጫና የሚቃወም ሰልፍ በደቡብ አፍሪካ በፕሪቶሪያ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሰልፈኞቹ በፕሪቶሪያ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ለኤምባሲውም ደብዳቤ አስገብተዋል።

በተመሳሳይም ፕሪቶሪያ በሚገኘው የአውሮፓ ሕብረት መስሪያ ቤት ተቃውሟቸውን እንደሚያሰሙና ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ተገልጿል።

በሰልፉ ላይ በደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን፣ ደቡብ አፍሪካውያንን ጨምሮ በአገሪቷ የሚኖሩ የተለያዩ አፍሪካ አገራት ዜጎችና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች እየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡

በሰልፉ ላይ ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ ለመጫን የሚፈልጉትን ዘመናዊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የሚቃወሙ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።

ሰላማዊ ሰልፉ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ የሚያሳዩበት እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጁት የተባበሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር በደቡብ አፍሪካ እና የአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ናቸው።