የምገባ መርሃ-ግብር ተግባራዊ መሆን ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ተግባራዊ መሆን በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በዘንድሮው ትምህርት ዘመን ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመያዝ በሁሉም የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ምገባ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልጿል።

በእያንዳንዱ ምርት ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ 80 ሚሊየን ብር መመደቡንም ጠቁሟል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ምህረት እንደተናገሩት፤ የመርሃ ግብሩ ተግባራዊ መሆን ወላጆች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር መጠነ መቋረጥ እንዲቀንስ አድርጓል።

በዚህም በ2013 የመርሃ ግብሩ አተገባበር ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ከ240 በላይ ተጨማሪ የመመገቢያና የማብሰያ አዳራሽ ተገንብተዋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ለሚሳተፉ 10 ሺሕ እናቶች የኮቪድ-19 ክትባት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

የምገባ መርሃ-ግብሩ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ40 ሺሕ በላይ ተጨማሪ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማድረጉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

የምገባ መርሃ-ግብሩ ጥቅም 1 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡

የተማሪዎች የደንብ ልብስ ትምህርት በተጀመረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተሰራጭቶ እንደሚጠናቀቅ ጠቅሰው፣ እስካሁን ባለው ጊዜ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደብተር ለተማሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል።

የደብተር አቅርቦቱ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የምገባ መርሃ-ግብሩ የወላጆችን ጫና ከማቃለሉ ባሻገር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉ በማድረግ ለሀገር ግንባታ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ተማሪዎች መንግስት የሚያቀርብላቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ወላጆች ተገቢውን ክትትል አንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ በ2013 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የወላጆች ክትትል አናሳ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የምገባ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ትምህርት ቤቶች በዘንድሮው ትምህርት ዘመን መርሃ ግብሩን ለመተግበር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የህብረት አፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አባተ ዘውዱ በትምህርት ቤቱ በመርሃ ግብሩ የሚሳተፉ እናቶች በምግብ አዘገጃጀትና በኮቪድ ስርጭት ዙሪያ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኒው ኢራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ ሃመረ ታደሰ በትምህርት ቤታቸው የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን፣ የመመገቢያ አዳራሾችን የማዘጋጀትን የማጽዳት ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከ520 ሺሕ በላይ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከ194 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያካትት ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።