የምግብ ዋስትና ጥያቄን ሊመልስ የማይችል የግብርና ስርዓት ሊኖር አይገባም – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) የምግብ ዋስትና ጥያቄን ሊመልስ የማይችል የግብርና ስርዓት ሊኖር እንደማይገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለፁ።

የአማራ ክልል የመኸር ምርት ቅድመ ዝግጅት የግምገማ መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።

በመድረኩም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት “አሁን ላይ የጦርነት ስጋት እና ሌሎች የፀጥታ ችግሮች ያሉብን በመሆኑ፤ ሁኔታው ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳያመራ የኢኮኖሚው መሰረት የሆነው የግብርና ዘርፍ እንዲሻሻል በቅንጅት መስራት ይገባል” ብለዋል።

“ለግብርና ምቹ የሆነ አቅም ቢኖርም አሁንም የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ አልቻልንም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂና ግብዓቶችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) በበኩላቸው በዚህ የመኸር ምርት ወቅት 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

እቅዱ እንዲሳካ በትጋት መስራት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።