የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ

ነሐሴ 1/2014 (ዋልታ) ምርታማነትን ለመጨመርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ማልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ አስገነዘቡ።
የሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች ዛሬ በወላይታ ሶዶ በተለምዶው ዲፖ እና ግብርና ኮሌጅ መካከል በሚገኘው ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነ ቦታ ላይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
በመርሃ ግብሩ ወቅት ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ እንዳሉት ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መትከል ጉልህ ሚና አለው።
ከውጪ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን እዚሁ በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ዜጎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩና ሌሎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መገኘታቸውን ገልጸው ችግኞች ጸድቀው አስፈላጊ ግልጋሎት እንዲሰጡ የመንከባከብ ሥራ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሺመቤት ነጋሽ በበኩላቸው በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል አለመሆኑን ገልጸዋል።
ችግኝ ተከላውም የኅብረተሰቡን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ በመሆኑ እነዚህና መሠል የተለያዩ ማኅበራዊ ድጋፎችን ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ከችግኝ ተከላው በመቀጠል የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራ እንደሚከናወን ታውቋል።