የምግብ ፍጆታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የካቲት 30/2014 (ዋልታ) የምግብ ፍጆታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በዋጋ ጭማሪና በኑሮ ውድነት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ያሉት ከንቲባዋ በተለይም  በከተማ አስተዳደሩ በመንግሥት ድጎማ እየተሰራጨ ያለውን የምግብ ዘይትና ዳቦ በተመለከተ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።

የምግብ ዘይት በህገወጥ ክምችት የተገኘውንም ጨምሮ በተለያዩ አቅራቢዎችም እንዲቀርብ በማድረግ ለጊዜው ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እየተሰራጨ በመሆኑ የከተማው ነዋሪ በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የምተዳደሩ በየአካባቢያቸው ወደሚገኙ የሸማች ሱቆች በመሄድ ምርቶቹን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

የሸገር ዳቦን በተመለከተ ፋብሪካው በእድሳትና በወቅቱ የስንዴ ዋጋ ንረት ምክንያት ለጊዜው ማምረት አቁሞ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ 613 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ እንዲሁም በ198 ሚሊዮን ብር ለስንዴ አቅርቦት በድምሩ 812 ሚሊዮን ብር በመመደብ  የዳቦ ምርት ማስጀመር ችሏል ብለዋል፡፡

ከነገ ጀምሮም ምርቱ ወደ ገበያ የሚወጣ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የሸገር ዳቦ በምናሰራጭባቸው ማዕከላት ዳቦ ማግኘት ይችላል ሲሉም አመልክተዋል።

ነገር ግን እነዚህ ምርቶች ዝቅተኛውንና በተለይም ቅድሚያ ወደሚሰጠው ሕዝብ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ ላይ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህንንም ለመቅረፍ  የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ቁጥጥር ቢኖርም ሕዝቡ በተለይም የዳቦ በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ  እየቀረበ ሳለ የተሻለ ገቢ ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ምርቱን ወስደው የሚያተርፉበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች ይጦቅማሉ ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኅብረተሰቡ ይህንን ሁኔታ በመጠቆም፣ በማጋለጥ እና በመቆጣጠር በኩል ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማችን የንግዱ ማኅበረሰብም በመተሳሰብ ለጊዜው ትርፋችሁን ቀንሳችሁ ሕዝባችሁን ታተርፋ ዘንድ ጥረት ማድረግ አለባችሁ ሲሉም አሳስበዋል።