የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የሁሉም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የመዲናዋን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የሁሉም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሥራ እድል ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት የ1ኛ ምዕራፍ የ3ኛ ዙር 5 ሺሕ 938 የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን አስመርቋል።

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በመርኃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር መድረኩ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት የሥራ ትጋት ስንቅ እንደሚሆን ጠቅሰው በከተማው የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚሰራው ሥራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ብቻውን ሥራ ፈጣሪ መሆን ባለመቻሉ የግሉ ዘርፍ ሊበረታታና ሊደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀማል ረዲ በበኩላቸው ተመራቂዎችም ሆነ አምራቾች የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን ለማቃለል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንደመሆኑ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመድረኩ ከተመራቂዎች የተሻለ የቆጠቡ፣ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ አምራቾች፣ ለሥራ ፈጠራ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሴክተሮች፣ ከፍተኛ አፈፃፀም ያመጡ ባለሙያዎችና ወረዳዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸውዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW