የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላት ለሚሯሯጡ ቡድኖች ተብሎ የሚፈርስ አገር የለም- ዶክተር አብርሃም በላይ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ

መጋቢት 1/2013 (ዋልታ) – የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላት ለሚሯሯጡ ቡድኖች ተብሎ የሚፈርስ አገር የለም ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን ከገነቡ ሕዝቦች አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ የሕዝብ ሳይሆን የቡድንና የግል አጀንዳ በማስቀደም አገር ለማበላሸት የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የእነዚህ ሕልመኞች ፍላጎት እንዳይሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ በመሆን የአገሩን አንድነት ለማስቀጠል መስራት አለበት ብለዋል።

‘ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን የሚጠናከረው ስንደጋገፍ ስንረዳዳና የአንዱ ችግር የሌላችን መሆኑን ስናረጋግጥ ነው’ ብለዋል።

አገር የሚገነባው በአብሮነት፤ ሲቸገር በመተጋገዝ ሲደሰት አብሮ በመደሰት ነው ያሉት ዶክተር አብርሃም ኢትዮጵያ አንድ አካል ነች አንገቷን መቁረጥ አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ አገር የመሰረተ፣ አገር ያጸና፣ ለአገር መስዋዕትነት የከፈለ ነው፤ ይህን የሚገፋ አካል ካለ ‘ታሪክ ያበላሻል’ ብለዋል።

ዶክተር አብርሃም የትግራይ ሕዝብ ሲቸገር ብቻችሁን የምትወጡት ችግር የለም በማለት ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ ክልሎች ሕዝቦችና አመራሮች ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።