የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ የሀረሪ ክልል መንግስት ገለጸ

ጥቅምት 27/2015 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል መንግስትና ህዝብ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ ገለጸ።
በተጨማሪም በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሀት መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ከሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ የተጠናቀቀ ነው።
የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል እና መንግስትና ህዝባችን ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ያስችላል።
መንግስት ከጅምሩም ቢሆን ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ ማሳየቱ የሚታወስ ሲሆን የሰላም ውይይቱም በአፍሪካ ህብረት እንዲካሄድ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘው አቋም ውጤት አምጥቷል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ መንግስትና በህውሃት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የአፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ በተግባር የታየበት ነው።
ከዚህ ባሻገር ስምምነቱ የሀገራችንን ሰላም እና የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲሆን የማይፈልጉ አካላትን አንገት ያስደፋ ሆኗል።
የሀረሪ ክልል መንግስትና ህዝብ በተደረሰው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ ከመደገፍ ባሻገር በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ለሚደረጉ ጥረቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ በአንድነት በመሰለፍ ድጋፉን ማሳየት ይገባል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሃት መካከል ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪውን ያቀርባል።
የሰላም ስምምነት በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ለደከማችሁና የህይወት ዋጋ የከፈላችሁ ሁሉ ታላቅ ክብር ይገባቹሀል።