የሰራተኞችን ጥቅምና መብቶች የማስከበርና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ሙፈሪሃት ካሚል


ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የሰራተኞችን ጥቅምና መብቶች የማስከበር እንዲሁም ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሣሁን ፎሎ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን በማስመልከት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው የሰራተኛውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በየጊዜው የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ምላሽ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰራተኞችን ጥቅምና መብቶች የማስከበር እንዲሁም ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሯ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የሥራ ላይ ደህንነት፣ መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የላቀ ብቃትና እውቀት፣ ክህሎትና ሁሌም ዝግጁነት ያለው ሠራተኛ የማፍራት ስራም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሣሁን ፎሎ በበኩላቸው የሠራተኞች መሰረታዊ ጥያቄዎች በሂደት ምላሽ እንዲያገኙ ከመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በነገው ዕለት በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135ኛ ጊዜ ይከበራል።