የሱዳኑ ጠ/ሚ/ር ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው መግለጫ

መስከረም 11/2014 (ዋልታ) በሱዳን የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ገለፁ፡፡

ሙከራው አገሪቱን በተለይም ምስራቃዊ ክፍሉን ሰላምና ደኅንነት ለመንሳት ያለመ ነበር ብለዋል፡፡

እንደ አልጀዚራ ዘገባ የሙከራው አቀናባሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ይዘው ረጅም ዓመታትን በመንበሩ የነገሱትና እሳቸውም በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት የኦማር አልበሽር አስተዳደር ተጠቃሚ የተባሉ ሰዎች ናቸው ተብለዋል፡፡

እውነታውን ለሕዝብ እናሳውቃለን የድርጊቱ ፈጻሚዎችም በሕግ ይጠየቃሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙከራው የሽግግሩ ሁኔታ በግልጽ መገመገም እንዳለበት ያመላከተ እንደሆነም ነው ያስታወቁት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሜጄር ጄኔራል አብደል ባቂ በክራዊ የተመራ ነው ስለተባለው ሙከራ በሰጡት መግለጫ የሽግግር ሂደቱን ለመጠበቅ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ገልፀዋል፡፡

የማክሰኞ ረፋዱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከሽፎ በተያዙ 40 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ መጀመሩንም ካርቱም አስታውቃለች፡፡

በሕዝቡ የዳቦና ነዳጅ ጥያቄ የምትናጠው ሱዳን መረጋጋት የተሳናት አገር ስትሆን መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥትም ከመፍትሔ ይልቅ በሲቪልና ወታደሩ እንዲሁም በወታደሩ ክንፍ መካከል እርስ በእርስ የማይተማመን ሆኗል፡፡