የሱዳን ታጣቂዎችና ሚሊሻዎች ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ጥቃት መፈፀማቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የሱዳን ታጣቂዎችና ሚሊሻዎች ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ጥቃት መፈፀማቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

ሚሊሻዎቹ  እና  ታጣቂዎቹ የገበሬዎችን ማሳ በመዝረፍ እና በማፈናቀል በርካታ ህገ ወጥ ድርጊት መፈጸማቸውን አምባሳደር ዲና ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሱዳን አመራሮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ በሀለቱ ሀገራት መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላትና ወደ ሱዳን የሸሸው የጁንታው ቡድን ሁኔታው እንዲባባስ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጥያቄ በአንዳንድ የሱዳን ፖለቲከኞችም ይስተዋላል ያሉት ቃልአቀባዩ፣ ድርጊቱን በመደገፍ በሱዳን የሚገኙ መገናኛ ብዙኃንም ሲያራግቡት መቆየታቸውን አንስዋል፡፡

ከሰሞኑ በሱዳን በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይም ብሔርን መነሻ ያደረገ ማጎሳቆል እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላት ሁኔታዎችን ለማባባስ እየሰሩ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)