የሲሚንቶ ገበያውን ለማረጋጋት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

ሚያዚያ 17/2914 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ “የተጋነነ እና ሕገ-ወጥነት የሚስተዋልበትን የሲሚንቶ ገበያ ለማረጋጋት፤ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል” ሲል አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙት  ናሽናል ሲሚንቶ እና ቱሬ ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ተዘዋውሮ ከጎበኘ በኋላ፤ ከፋብሪካዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዚሁ የመስክ ምልከታቸው፤ የናሸናል ሲሚንቶ እና የቱሬ ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበሮች፤ አንዱን ከረጢት ሲሚንቶ እስከ 4 መቶ 40 ብር ብቻ እንደሚሸጡ ተረድተዋል።

ይሁን እንጂ ከፋብሪካዎቹ በዚሁ ተመን የሚወጡት እነዚሁ ምርቶች፤ እስከ 1 ሺህ 2 መቶ ብር እና ከዚያ በላይ የሚሸጡበት ሁኔታ፣ በባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ፋብሪካው ጥሬ ዕቃ በሚያገኝበት ቦታ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እየተደረገ ስለመሆኑም፤ የየፋብሪካው አመራሮች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት በተጨማሪነት አስረድተዋል።

የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ  እግዝኤል ብዙአየሁ እንደጠቆሙት፤ ገበያን በማረጋጋት ረገድ መንግስት ክትትል እና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡

የዘርፉን የምርት አቅርቦት እና ፍላጎት ለማመጣጠን አክሲዮን ማህበሩ በተለያዩ አካባቢዎች የጀመራቸው አዳዲስ ፕሮጄክቶች በመንግሥት እንዲደገፉም ጥያቄያቸውን አያይዘው አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የቱሬ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጥሬ እቃዎችን ጭኖ ወደ ፋብሪካው ለመውሰድ በአንድ መኪና እስከ 100 ብር በሕገ-ወጥ መንገድ ለግለሰቦች እየከፈለ ስለመሆኑ፤ የፋብሪካው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዚዳይዳን በክሪ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልፀዋል።

የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ፤ የተጠቀሱትን ችግሮች ሁሉ ፋብሪካዎቹ ከአስተዳደሩ እና ከማኅበረሰቡ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሆነው ሊፈቷቸው እንደሚችሉ አስገንዝቧል፡፡

ከዚህ በዘለለ ግን ፋብሪካዎቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እያበረከቱ ያለው ሁለገብ አስተዋጽዖ የሚደነቅ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ  በጋሻው ተክሉ አውስተው፤ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል የማስፋፊያ ሥራ ግን በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባው አመላክተዋል።

የድሬደዋ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ደግሞ፤ መስተዳድሩ ለኢንዱስትሪ እና ለፋብሪካዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሀብት ለማወቅ እና ለመጠቀም የማዕድን ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ማስረዳታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።