የሲዳማ ክልል የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጹ።

የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሀዋሳ ከተማ ሶሬሳ ጉዱማሌ እየተከበረ ሲሆን ርዕሰ መስተዳድሩ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የፊቼ ጫምባላላ በዓል እርቅና ሰላም የሚሰፍንበት እንዲሁም አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

የፊቼ ጫምባላላ በዓል እሴቶች በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለተጀመረው ምክክር በግብዓትነት የሚጠቅም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ እሴትን በጠበቀ መልኩ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ እንደቆና ይህንን መልካም ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሲዳማ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የሲዳማ ሕዝብ የረዥም ዘመናት ጥያቄ የነበረው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁንም የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ እና ለዚህም ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በፊቼ ጨምባላላ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጽያ እየታዩ ያሉ የብሔር እና የሃይማኖት ፅንፈኝነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዚህ አይነቶቹን ኋላ ቀር አስተሳሰቦች በመታገል እና በመቻቻል የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

በኃይሉ ጌታቸው (ከሀዋሳ)

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!