የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የጅቡቲ የሚኒስትሮች ቡድን የኢትዮ ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የውሀ ፕሮጀክትን ጎበኙ

 
ሰኔ 23/2013 (ዋልታ) – የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኢብራሂም ኡስማን ከጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አብዲቃድር ካሚል ከተመራው የጅቡቲ ከፍተኛ የሚኒስትሮች ቡድን ጋር በመሆን በሲቲ ዞን ሀዲጋላ ወረዳ በሚገኘው የኢትዮ ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የውሀ አቅርቦት ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱ ፕሮጀክቱ ያለበትን ሁኔታ በመመልከት በቀጣይ ፕሮጀክቱ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ሲሆን ከጅቡቲ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኢብራሂም ኡስማን ጉብኝቱ በሲቲ ዞን የሚገኘውን የኢትዮ ጅቡቲ የውሀ አቅርቦት ፕሮጀክትን በመመልከት ፕሮጀክቱ ያሉበትን ጥቃቅን ከፍተቶች በመፍታት በቀጣይ ፕሮጀክቱ በተሻለ ሁኔታ ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ በተለያዩ የኢኮኖሚ ፣ የመሠረተ ልማትና ማህበራዊ መስኮች ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው የጠቆሙት ምክትል ርእስ መስተዳደሩ ይህ ድንበር ተሻጋሪ የውሀ አቅርቦት ፕሮጀክት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ በቀጣይ ፕሮጀክቱ የሚሰጠውን የውሀ አቅርቦት ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
የጅቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አብዱቃድር ካሚል በበኩላቸው የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የውሀ አቅርቦት ፕሮጀክትን አገልግሎቱንና አቅሙን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ስኬታማ ጉብኝትና ወይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከተጀመረ 8 አመት የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮጀከት በቀን መቶ ሜትር ኪዮብ ውሀ ወደ ጅቡቲ ለማሰራጨት ታልሞ የተገነባ ፕሮጀክት ሲሆን ፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች 60 ሜትር ኪዩብ ውሀ ብቻ ለማሰራጨት መቻሉን በጉብኝቱ ወቅት መገለጹን የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ዘግቧል፡፡