የሸዋል ኢድ በዓል ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን ያጠናክራል – ኦርዲን በድሪ

ሚያዝያ 30/2014 (ዋልታ) የሸዋል ኢድ በዓል ከሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ባለፈ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን ያጠናክራል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
በክልሉ የሸዋል ኢድ በዓል የማስጀመሪያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ ርዕሠ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት” አካል የሆነው የሸዋል ኢድ በዓል ዲያስፖራዎች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ እንግዶች፣ አምሰቱ የአጎራባች ክልሎች እና ሌሎች አካላት በዓሉ ተሰባስበው ማክበራቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ አንዱ የሌላውን ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶች ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ ያስችላል።
ከዚህ በተጨማሪም የባህል፣ የቅርስና የቱሪዝም ሃብቶቻችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማበልፀግ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አሟጦ ለመጠቀም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
የሸዋል ኢድ በዓል “ከኢድ እስከ ኢድ” መርኃ ግብር ጋር ተቀናጅቶ መካሄዱ በዓሉን የሚያደምቀውና በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራል ብለዋል።
የመድረኩ የክብር እንግዳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው ለታሪካዊ ቅርሶች ባህሎች ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
አንድነትና ፍቅርን በማጎልበት እና መልካም እሴቶችን በማጠናከር ሀገራችን ማሻገር ይገባል ያሉት ደግሞ “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት” መርኃ ግብር ጣምራ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው።
ኡስታዝ አቡበከር መሰል ባህላዊ እሴቶችም እርስ በእርስ ያለንን ትስስርን ከማጠናከር አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በመክፋቻ መርኃ ግብሩ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
ተስፋዬ ሀይሉ (ከሀረር)