የቀድሞው የአልሸባብ መሪ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

ሙክታር ሮቦው

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የአልሻባብ ሁለተኛ ሰው የነበሩት ሙክታር ሮቦው በሶማሊያ የኃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

በአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙደ አስተዳደር ውስጥ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሮቦው የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሆነውም አገልግለዋል።

እ.አ.አ በታኅሣሥ 2018 ለደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ክልል አስተዳዳሪነት የምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ ታስረው ለቁም እስር መዳረጋቸውን ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ እ.አ.አ ነሐሴ 2017 ለሶማሊያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተው እንደነበርና ይህም ከአልሻባብ የከዱ ከፍተኛው አባል እንዳደረጋቸው አመላክቷል።

በወቅቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስመልክቶ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሮቦው በባይዶዋ ሚሊሻዎችን ሲያደራጁ ነበር ብሏል።

የወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት ሮቦው ከጽንፈኛ አመለካከታቸው አልተላቀቁም የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር። መታሰራቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ሙክታር ሮቦው የርዕዮተ ዓለም ልዩነትን በመጥቀስ ከአልሻባብ መውጣታቸውን በ2015 በማሳወቅ በኋላም ቡድኑን የሚዋጋ የራሳቸውን ቡድን ማቋቋማቸው ተጠቅሷል።

አንዳንዶች ይህ በአልሻባብ ላይ የርዕዮተ ዓለም ጦርነት ማወጅ ሊሆን ይችላል ቢሉም ሌሎች ደግሞ የአል-ቃኢዳ ተባባሪ በሆነው ቡድን አመራር ሆነው ሳለ በእሳቸው ስር ለተፈጸሙ ወንጀሎች መሸፈኛ አድርገውም ይመለከቱታል።

አልሻባብ በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ጥቃቶችን ይሰነዝራል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW