የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ በሰላም ተከበረ

የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ

ታኅሣሥ 19/2015 (ዋልታ) የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የምስራቅ ሐረረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የፀጥታ ኃይሉ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ጉልህ ድርሻ እንዳበረከተ ተጠቁሟል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ናስር መሀመድ እንደገለጹት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ከሀገር ውስጥና ከወጭ የመጡ ምዕመናን እና ሌሎች እንግዶች የታደሙበት የዘንድሮው በዓለ ንግስ በደመቀ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።

የበዓሉ አከባበርም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ለዚህም በስፍራው የተሰማራው የጸጥታ ኃይል ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አመልክተዋል።

የዘንድሮ ንግስ በዓል በተለየ መልኩ ካለምንም ትራፊክ አደጋና የወንጀል ድርጊት ነፃ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዓሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በበዓሉ ላይ የተገኙ ምዕመናን ፈጣሪያቸውን በማመስገን ወደ የመጡበት አካባቢ በመመለስ ላይ ናቸው።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)