የቁልቢ ገብርኤል በዓለ ንግስ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ


ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) –
የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ ያለምንም የፀጥታ ችግር እና የትራፊክ አደጋ እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በዓለ ንግሱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ለማስቻል ለሁሉም ፈፃሚ አመራር እና አባላት እንዲሁም አጋዥ ተቋማት በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከማድረግ ጀምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸው ተመላክቷል፡፡
በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግርና የትራፊክ አደጋ በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ ለማስቻል በስውርና በግልፅ የሰው ሃይል በመመደብ ወደ ስራ መገባቱ ነው የተገለጸው፡፡
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች ራሳቸውን ከተለያዩ የስርቆትና ሌሎች መሰል የወንጀል ድርጊቶች መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
እንግዶች የተለዩ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥማቸውም ወዲያውኑ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
ለበዓሉ ሰላማዊነት ሁሌም ከፖሊስ ጋር ተባብሮ የሚሰራውና ለሰላሙ ቅድሚያ የሚሰጠው መላ የአስተዳደሩ ነዋሪ አሁንም ከፖሊስና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጎን በመሆን ይበልጥ አብሮ እንዲሰራ ጥሪ መቅረቡን ከአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡