የበረራ ደህንነትን ማረጋገጥ የአየር መንገዶች ብቻ ሳይሆን የመንገደኞችም ኃላፊነት ነው – ባለስልጣኑ

 

ነሀሴ 23/2016 (አዲስ ዋልታ) የበረራ ደህንነትን ማረጋገጥ የአየር መንገዶች ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመንገደኞች ጭምር መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች የአየር መጓጓዣ ተሳፋሪ መንገደኞች ሊተገብሯቸው የሚገቡ የስነ ምግባር ግዴታዎችን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመስጠት ያለመ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከተቋሙ የአቪዬሽን ሪጉሌሽን እና ከኤርናቪጌሽን ዘርፍ የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች እንዳሉት በአውሮፕላኖች ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጨዋነት የጎደላቸው እና የሚረብሽ ባህሪያት መልካም ስርአትን እና ዲሲፕሊንን የሚጎዱ ከመሆናቸውም ባሻገር አየር መንገዶች መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፉ ናቸው፡፡

ባለስልጣኑ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራት መካከል የበረራ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ የበረራ ቁጥጥር ስራዎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ እነዚህ የቁጥጥር ስራዎች ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ያስቀመጣቸውን መስፈርቶችና ስታንዳርዶች መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው፡፡

እነዚህ መስፈርቶችና ስታንዳርዶች አየር መንገዶች በጥንቃቄ ሊተገብሯቸው የሚገቡ አሰራሮችን የሚያመለክት ሲሆን የቁጥጥር ስርዓቱ ዋንኛ ዓላማም የበረራ ደህንነትን በማረጋገጥ የተሳለጠ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡
የጋዜጣዊ መግለጫውም ዋንኛ ትኩረት መንገደኞች የተጣለባቸው ኃላፊነቶችና ማግኘት የሚገባቸውን መብቶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እነዚህን አለም አቀፍ ህጎችና አሰራሮች ሳይሸራረፉ መተግበራቸውን ዕለት ተዕለት የሚከታተልና የሚቆጣጠር ተቋም እንደመሆኑ ከተሳፋሪዎች የሚጠበቁ ህጋዊ ግዴታዎችና ኃላፊነቶችን እንዲያውቁት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ከነዚህ ህጎችና ደንቦች ውስጥ ተሳፋሪዎች ሊከተሏቸው ከሚገቡ ህጎችና ደንቦች ውስጥ የአየር መንገዶች ሰራተኞችና የሚያስተላልፉትን መመሪያና ደንቦች ተቀብሎ መተግበር መሆኑን አሳስቧል።