‘የበቃ’ ዘመቻ አካል የሆነው ሰልፍ በአሜሪካ ዴንቨር ከተማ ተካሄደ

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) ‘የበቃ’ ወይም #NoMore ዘመቻ አካል የሆነው ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት በምትገኘው ዴንቨር ከተማ ተካሄደ።

የትናንቱ ሰልፍ መነሻውን  ‘ካፒቶል ሂል” እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ በማድረግ ወደ ‘9ኒውስ’ የቴሌቪዥን ጣቢያና ወደ ዴንቨር ከተማ ማዕከል በማቅናት ተካሂዷል።

በሰልፉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሳተፉ ሲሆን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበሉና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ከአስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ማክበር ይገባታልም ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስት አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የፈጸመውን ወረራ በማውገዝና እርምጃ በመውሰድ ከእውነት ጎን መቆም እንደሚገባው አመልክተዋል።

የምዕራቡ ዓለም አገራት በአፍሪካ ላይ ለመጫን የሚፈልጉትን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አፍሪካውያን አይቀበሉትም ነው ያሉት ሰልፈኞቹ።

ሰልፈኞቹ በዴንቨር ከተማ በሚገኘው ‘9ኒውስ’ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የሚደግፉ የፕሮፓጋንዳ ዘገባዎችን እያወጣ እንደሚገኝና ጣቢያው ይህን አፍራሽ ተግባሩን ማቆም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።