የበቆሎ ማሳውን ለመታደግ የሞከረ ግለሰብ በዝሆን ጥቃት ህይወቱ አለፈ

ሚያዝያ 12/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮንታ ዞን የበቆሎ ማሳውን ለመታደግ የሞከረ ግለሰብ በዝሆን ጥቃት ህይወቱ ማለፉ ተገለጸ፡፡

የኮንታ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ባሳ በየነ እንደገለጹት በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ ሴሬ ቀበሌ ትናንት ምሽት 4:00 ሰዓት ሟች የበቆሎ ማሳውን ከዝሆን ለመጠበቅ ሲሞክር ነው በድርጊቱ በተቆጣው ዝሆን ጥቃት ህይወቱ ያለፈው።

ጥቃት አድራሹ ዝሆን አርሶ አደሩን በኩምቢው በመያዝ በእግሮቹ በመርገጡ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏልም ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ጎሽ ተመሳሳይ ጥቃት አድርሶ እንደነበር ያስታወሱት ዋና አዛዡ ኅብረተሰቡም ራሱን ከመሰል አደጋ እንዲጠብቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW