የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር “ጥበብ ለእናት ሀገር” የተሰኘ መርኃግብር አስጀመረ

ነፊሳ አልማሃዲ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሀገሪቱ በምትገኝበት የኅልውና ጦርነት ድርሻውን ለመወጣት “ጥበብ ለእናት ሀገር” የተሰኘ መርኃግብር ማስጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ለጀግናው ሕዝባዊ ሠራዊት ስንቅ ማዘጋጀት፣ ደም መለገስ፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ ማሠባሠብ፣ በጦርነቱ ቆስለው በሆስፒታል የሚገኙ የሰራዊቱ አባላትን መጎብኘት እና ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ሚኒስቴሩ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸው ተጠቁሟል።

“ጥበብ ለእናት ሀገር” በተሰኘው መርኃግብር ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የሙዚቀኞች፣ የአርቲስቶች እና ሰዓሊያን ማህበራት እንደሚሳተፉበት ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከሚኒስቴሩ ወደ ግንባር የሚዘምቱ ዘማቾች ዛሬ ከሰዓት ሽኝት የሚደረግላቸው ሲሆን በዛሬው እለት የተለያዩ ተግባራት በይፋ ይጀመራሉ ተብሏል።

ኅዳር 26/2014 ዓ.ም በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በተከፈተ የባንክ አካውንት ገቢ የሚደረግ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ እንደሚከናወንም ተገልጿል።

“ዛሬን ለሀገሬ” በተባለ ሕዝባዊ ንቅናቄ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ከያኒያን እና ኮሜዲያንን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃግብር ይደረጋልም ነው የተባለው።

በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ሰዎችን ወደ ግንባር ይዞ በመሄድ ለሀገሩ እየተዋጋ ያለውን ሕዝባዊ ሰራዊት የማነቃቃት እና የማበረታታት ስራዎችን ለመከወን ሚኒስቴሩ ዝግጅት ማጠናቀቁን መግለጫውን የሰጡት የኪነጥበብ፣ ስነ ጥበብ እና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ አስታውቀዋል።

በትዝታ ወንድሙ