የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ርብርብ ያስፈልጋል ተባለ

ሚያዝያ 25/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ መረባረብ እንዳለበት ተገለፀ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር በዛሬው ዕለት ሀገር ዐቀፍ ጉባኤ ከሪል ስቴት አልሚ ድርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ሚኒስቴሩ በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በቤት ልማት ሥራ በከተማ ቤት ልማት ንዑስ ፕሮግራም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም በገጠር የቤት ልማት ንዑስ ፕሮግራም 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚደርሱ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተመላክቷል፡፡

የመኖሪያ ቤት እጥረት ብሎም ከአቅም በላይ የሆነ የዋጋ ንረት ነዋሪውን እያስጨነቀ ያለ ተግዳሮት ሲሆን ጥራት ያላቸውን ቤቶች ለነዋሪዎች ለማመቻቸት እየሰራ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ከሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የቤት መሰረተ ልማት መገንባት እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል።

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ባጠናው ጥናት መሰረት በሀገሪቱ ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በዓመት 381 ሺሕ ቤቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅትም 74 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ከጥራት ደረጃ በታች እንደሆኑም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

1 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለውን የሪል ስቴት ቤቶችን ብሎም በግል እና በመንግሥት ባንኮች በማይክሮ ፋይናንስ ያለውን አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ተገልጿል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚታየውን የቤት ችግር ለመቅረፍ 80 በመቶ የግል ዘርፉን ተሳታፊ በማድረግ እንደሚሰራም በመድረኩ አመላክቷል።

ከከተማ ልማት ባሻገር ፍልሰትን ለመከላከል የገጠር መሰረተ ልማትን በማጠናከር ጥራት ያላቸውን ቤቶች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁማል።

በመድረኩ የከተማ መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

በሀኒ አበበ

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!