የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የ2014 በጀት 5.8 ቢሊዮን ብር እንዲሆን አጸደቀ

ሐምሌ 16/2013(ዋልታ) – የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት በቀረበው የበጀት ረቂቅ ላይ በመወያየት ለ2014 በጀት ዓመት የሚውል 5 ቢሊዮን 890 ሚሊዮን 442 ሺህ 89 ብር አድርጎ አጸደቀ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን የተለያዩ የማሻሻያ አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡

ለበጀት ዓመቱ እንዲውል ከተያዘው በጀት ውስጥ 1 ቢሊዮን 855 ሚሊዮን 951 ሺህ 147 ብር በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን፣ 3 ቢሊዮን 542 ሚሊዮን 958 ሺህ 540 የሚሆነው ከፌዴራል መንግሥት በድጎማ፣ ቀሪው ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት የውስጥ ገቢ፣ ከዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ እንዲሁም ከውጪ ከሚገኝ ዕርዳታ የሚገኝ ነው፡፡

በምክር ቤቱ ከጸደቀው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 219 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የሚሆነው ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ የሚውል መሆኑም ተገልጿል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ለበጀት ዓመቱ ስራ ላይ እንዲውል የጸደቀው በጀት፣ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማልማትና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሃብት አኳያ በዕቅድ ከተያዘው በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደሚጠበቅም የምክር ቤት አባላቱ አመልክተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በ2ኛ ቀን የጉባዔ ውሎው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2013 ዓ.ም ዓመታዊ አፈጻጸም በማድመጥ ከተወያዬ በኋላ መርምሮ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ የክልሉ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የማሻሻያ አዋጅን መርምሮ በማጽደቅ 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማጠናቀቁን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።