የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በምዕራብ ወለጋና በጋምቤላ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ

ሰኔ 18/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በምዕራብ ወለጋና በጋምቤላ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ።
 
የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
 
አባላቱ ጥቃቱን አውግዘው በቀጣይ የጥቃቱን ተጎጂዎች ከመደገፍ ጎን ለጎን ህግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
 
የማዕከላዊ ኮሚቴው አባልና የመስኖና ቆላማ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ፤ ሸኔና ሌሎች አሸባሪ ኃይሎች ሀገርን ለማፍረስ ብዙ ጊዜ ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር በንጹሃን ላይ የፈፀሙት ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል።
 
አሸባሪ ኃይሎቹ በተቀናጀ መንገድ የፈጸሙትን ዘግናኝ እልቂት የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ በፅኑ ማውገዙን ነው የገለጹት።
 
ሌላኛው የኮሚቴው አባል ግርማ አመንቴ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው በንጹሃን ላይ የተፈፀመውን እልቂት ማውገዙን በማንሳት ፅንፈኞች የሀገሪቱን አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚንድ አስነዋሪ ድርጊት ፈፅመዋል ነው ያሉት።
 
ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ልብ የሚሰብር ነው ያሉት ሌላኛው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዛዲግ አብርሃ ናቸው።
 
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ኡሞድ ኡጁሉ፤ ሸኔ፣ እራሱን የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድንና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ሰሞኑን በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሁሉንም ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
 
ድርጊቱን የፈጸሙ ኃይሎች ላይ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ህግ የማስከበር እርምጃው እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በዛሬው የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባም እየተወሰዱ ያሉ ህግ የማስከበር እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።
 
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዴዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በየአካባቢው ያሉ አደረጃጀቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመናበብ በአሸባሪ ኃይሎች ጋር የሚወሰደው እርምጃ እንዲጠናከር ማዕከላዊ ኮሚቴው መግባባት ላይ ደርሷል ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚና የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ፍስሐ ይታገሱ እንዲሁ የሽብር ቡድን አባላትን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድና ለህግ ከማቅረብ ባሻገር፤ ሕዝቡም በተደራጀ መንገድ እራሱን የሚከላከልበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ በስብሰባው መነሳቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ማሞ ምህረቱ፤ ፅንፈኝነትና አክራሪነትን ለማክሰም በትኩረት እንዲሰራና የፀጥታ ኃይሉም ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በተጠናከረ መንገድ እንዲጠብቅ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ እና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሎሚ በዶ፤ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመዋጋትና ለሰላም ዘብ በመቆም ሁሉም ዜጋ የሰላም አምባሳደር መሆን አለበት ብለዋል።
 
“አመራሩም የሚናገረውን የሚተገብርና አንድ መሆን አለበት” በማለት ለዚህም በአካባቢ ሳይታጠር የፀጥታ ችግሮችን በጋራ መፍታትና ተጠያቂነትን በአግባቡ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
 
ማዕከላዊ ኮሚቴው በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎችና የፓርቲ ሥራዎች ላይ ተወያይቶ በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት ላይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።