የብልጽግና ፓርቲ እና የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ እና የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እና በቅርቡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሊዩ ጂያንቾኦ የዌብናር ውይይት አድርገዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ለቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሊዩ ጂያንቾኦ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቻይና እየተመዘገበ ላለው ስኬት የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲን አመራር አድንቀዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲም ሀገር በቀል ፖሊሲዎችን በመተግበር ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው በሂደቱም ከቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ልምዶችን ሲቀስም መቆየቱንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

አሁን በምንገኝበት ሀገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ አንድነትንና ትብብርን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ አንስተው ሁለቱ እህት ፓርቲዎች ተግባር ተኮር የሆነ ግንኙነታቸውን በማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባቸው አውስተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክም የባለብዙ ትብብር ማዕቀፎችን በማጠናከር ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በዓለም እንዲሰፍን ከቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊዩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዋናዋ ምሰሶ እንደሆነች ቻይና እንደምታምን እና የብልጽግና ፓርቲም በቀጣናዊ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች አጋር እንደሆነ አመላክተዋል።

የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳደግ በቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ በኩል ጠንካራ ፍላጎት መኖሩን አንስተው የሁለቱን ፓርቲዎች የወደፊት የትብብር መስኮች ጠቅሰዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተስማሙ ሲሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችንም በቅርቡ እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW