የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባን ተከትሎ የተሰራጨው የድምፅ መልዕክት የውስጥና የውጭ አካላት ያቀናበሩት ተግባር ነው – ፓርቲው

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባን ተከትሎ ሾልኮ ወጣ ተብሎ የተሰራጨው የድምፅ መልዕክት የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የውስጥ እና የውጭ አካላት ያቀናበሩት ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲል የብልፅግና ፓርቲ ገልጸ፡፡
ፓርቲው በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ የፓርቲው ፕሬዝዳንት በስብሰባው ላይ ተናገሩት ተብሎ የተለቀቀው መረጃ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ላይ የተናገሩትን በመውሰድ እና በመቀጣጠል ሀላፊነት በጎደላቸው አካላት የተሰራጨ እና መሰረት ቢስ ነው ብሏል።
የፓርቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ጥቅማችን ተነካ ብለው የሚያስቡ እና የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የውስጥ እና የውጭ አካላት ኢትዮጵያን ከእድገቷ ለማሰናከል መስራታቸውን አያቆሙም ብለዋል።
እንዲህ ያሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትም በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመን ለመሸርሸር እና ጥርጣሬን በማስረፅ ግጭት ለማስነሳት የተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ እንዲህ ያሉ አንድነትን የሚሸረሽሩ መረጃዎችን በጥንቃቄ መርምሮ እና ምንጮቹን አጣርቶ መውሰድ ይኖርበታልም ብለዋል።
በማህበራዊ የትስስር ገፅ የሚለቀቁ መረጃዎችን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ከመቆጣጠር አንፃር ሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር አዋጅን ከማውጣት ጀምሮ አበረታች እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ቢሆንም ለቁጥጥር አመቺ አለመሆናቸው ስራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
በመሆኑም ጉዳዩን በህግ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ህብረተሰቡ በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚለቀቁ መረጃዎችን ከመውሰዱ በፊት ከትክክለኛ ምንጩ በማጣራት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
(በትዕግስት ዘላለም)