የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ፓርቲው በአደረጃጀት ጠንክሮ የሚወጣበት እንደሚሆን ተጠቆመ

የካቲት 30/2014 (ዋልታ) የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ፓርቲውን በብቃት የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች የሚመረጡበት እና ፓርቲውም ጭምር በአደረጃጀት ጠንክሮ የሚወጣብት እንደሚሆን የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

አሁን ላይ ፓርቲው በብዙ ስኬቶች እና ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ የጉባኤውን እለት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲው ለሦሥት ቀናት በሚያካሂደው ጉባኤ የተለያዩ አቅጣጫዎችን ከማስቀመጥ ባለፈ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ማለታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ከዚህ ባለፈም ፓርቲው የሚያስቀምጣቸውን እና የሚወስናቸውን ውሳኔዎች በሚገባ ማስፈፀም የሚችሉ ትክክለኛ እና ታማኝ መሪዎችን በመለየት እንደሚመርጥም ጠቁመዋል፡፡

ከጠቅላላ ጉባኤው በኋላም ፓርቲው የመረጠውን ሕዝብ ለማገልገል ካለፈው ስህተቱ በመማር እና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል በዋናነት በነገ ላይ ትኩረት አድርጎ በልዩነት፣ በአደረጃጀት እና በአስተሳሰብ ጠንክሮ እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡