የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የሙከራ ሥራ እየተከናወነ ነው

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ህጎችን ባከበረ መልኩ የሙከራ ሥራው እየተከናወነ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የብሔራዊ መታወቂያ የሙከራ ሥራ ያለበትን ደረጃ በመመልከት ከፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል።
ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ በተለያዩ የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ላይ እየተተገበረ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ ዘሚካኤል በ2018 ዓ.ም ህፃናትን ሳይጨምር 95 ከመቶ ለሚሆኑ ዜጎች መታወቂያውን ለማዳረስ ይሰራል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ፍትሃዊ አሰራርን ለመዘርጋትና ዜጎች በኦንላይን አገልግሎት ላይ ያላቸውን እምነት ለመጨመር ብሔራዊ መታወቂያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ለዜጎች የመረጃ ጥበቃ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለፕሮጀክቱ ስኬት ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
መታወቂያው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀውንና በመጽደቅ ሂደት ላይ ያለውን የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ የሚደነግጋቸውን ህጎች ባከበረ መልኩ የሙከራ ሥራው እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።