የብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በናይሮቢ፣ ጁባ እና ባህሬን የኢፌዴሪ ኤምባሲዎች ተከብሯል፡፡

የብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በናይሮቢ፣ ጁባ እና ባህሬን የኢፌዴሪ ኤምባሲዎች ተከብሯል፡፡
የዘንድሮ ሰንደቅ አላማ ቀኑ “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉአላዊነት ለሰንደቅ አላማችን ከፍታ’’ በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን፣ በስነ ሥርዓቱ ላይ የኤምባሲዎቹ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በናይሮቢ በተከበረው በዓል ላይ እንደተናገሩት የዘንድሮ በዓል የምናከብረው በአገራችን ሉአላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ በጋራ ለመከላከልና በተሰማራንበት የዲፕሎማሲ ዘርፍ የተሻለ ስራ ለማከናወን ቃል በመግባት ነው፡፡
አገራችን የጀመረችው የአዲስ ምዕራፍ ዲሞክራሲ እና የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ ከውስጥ እና ከውጭ በተቀናጀ መልክ የሚደረገውን ተፅዕኖ በአንድነትና በመደመር መንፈስ መመከት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ተሳታፊዎችም አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ለኢትየጵያ ብልጽግና ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን ጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ጊቢ የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች፣ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅ/ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
አምባሳደር ነቢል ማህዲ ሰንደቅ ዓላማ የብሄራዊ አንድነት መገለጫ፣ የብሄራዊ ፍቅርና ብሄራዊ ስሜት የሚገለጽበት፣ የሀገራዊ ህብረት አርማና ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ በዓሉ በሀገራችን በተሳካ ሁኔታ አዲስ የፖለቲካ ባህል ያረጋገጠ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያካተተ መንግስት በተመሰረተበት ማግስት የሚከበር ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉአላዊነት መከበር እያደረጉ ያሉትን ድጋፍና እያሳዩት ያለውን ቁርጠኝነት አመስግነው፣ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይም የሰንደቅ አላማ ቀን በባህሬን የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽ/ቤት ሲከበር የጽ/ቤቱ መሪ አምባሳደር ጀማል በከር ለታዳሚዎቹ ባደረጉት ንግግር በዛሬው ቀን በሰንደቅ አላማችን ፊት የአገራችንን ብሔራዊ ደህንነትና ክብር ለመጠበቅ እንዲሁም አገራችን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገውን አዲስ የዲሞክራሲ፤ የልማትና የብልፅግና ምዕራፍ ለማሳካት ሁላችን የተጣለብንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ቃል የምንገባባት ቀን ነው ብለዋል፡፡