የቦንጋ የኒቨርሲቲ ቅዳሜ ተማሪዎቹን ያስመርቃል

የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሃግብር ያሰለጠናቸውን 840 ተማሪዎች የፊታችን ቅዳሜ እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ2010 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 512 ወንድና 328 ሴት በድምሩ 840 ተማሪዎችን ነው የሚያስመርቀው፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች አስቸጋሪውን የኮሮና ወቅት አልፈው ለምርቃት በመብቃታቸውና በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ተመራቂዎች በመሆናቸው መደሰታቸውን ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ከማስመረቅ ጎን ለጎን የመማር ማስተማር ሥራውን ለማስፋት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው ማህበረሰብ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በተገቢው መንገድ እንዲካሄድ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግም ዶክተር ጴጥሮስ ጠይቀዋል፡፡

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሚሊዮን ዓለሙ በበኩላቸው፣ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የተሳካ እንዲሆንና የከተማዋን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎቹን እንደሚያስመርቅም ተጠቁሟል፡፡
(በነስረዲን ኑሩ)