የተሳሳቱ መረጃዎች የኮቪድ በሽታን የመከላከል ሥራ ከባድ እያደረገ ነው ተባለ

ታኅሣሥ 5/2014 (ዋልታ) በጤና ሳይንስም ይሁን በሃይማኖት አስተምሮ ተቀባይነት የሌላቸው መረጃዎች የኮቪድ በሽታን የመከላከል ስራን ከባድ እያደረገው ነው ተባለ።

ኮቪድ-19 በኤች አይ ቪ ኤድስ የማከም ሂደት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅእኖ እና በሃይማኖታዊ አስተምርሆ ለመከላከል የሃይማኖት መሪዎች ሚና በሚል ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኅብረተሰቡን የማስተማር እና የማንቃት ሥራን እያከናወነ እንዳለ አመላክተዋል፡፡

በተለይም የኤች አይቪ ኤድስ እና የኮቪድ 19 ወረረሽኝን ስርጭት አስመልክቶ ጉባኤው ሠፊ ስራን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ይሁን እና በጤና ሳይንስም ይሁን በሃይማኖት አስተምሮ ተቀባይነት የሌላቸው መረጃዎች የበሽታዎቹን የመከላከል ሥራን ከባድ እያደረገው በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን ሲሉም አንስተዋል።

በጉባኤው በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዓለም ላይ ከ5.3 ሚሊየን በላይ ሠዎችን በሞት የነጠቀው የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን ሊያደርስ ከሚችለው አስከፊ እና ከባድ ጉዳት የሃይማኖት ተቋማት ሕዝቡን በማስተማር እና በማሳወቅ ታድገውታል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ6ሺ 800 በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ኢትዮጵያን እስከወዲያኛው ያሳጣው ወረርሽኙ አሁንም በፍጥነት እየተሰራጨ ያለ በመሆኑ የመከላከል ሥራው አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ተስፋ ሠጪ የሆነውን የኮቪድ ክትባትን በተዛባ ሁኔታ ማየት የክትባት አገልግሎቱ በሀገሪቱ በተሳካ ሁኔታ እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል ያሉት ሚኒስትሯ እስካሁን ከ10.5 ሚሊየን ዶዝ ክትባትን ወደ 9 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ መውሠዱን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከበሽታው ስርጭት አኳያ በቂ ባለመሆኑ ስለክትባቱ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ማረም ይገባልም ብለዋል።

ከኮቪድ ባልተናነሰ ሁኔታ የኤች አይቪ ስርጭት ምጣኔው አሁንም እየጨመረ ያለ በመሆኑ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

ሀገሪቱ ያለችበትን አስከፊ ጊዜን ለማለፍ የሃይማኖት ተቋማት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው የተፈናቀሉ ወገኖች ለጤና እክል እና ሌሎች ችግሮች እንዳይዳረጉ ሊረባረቡ ሚኒስትሯ አክለዋል።

በድልአብ ለማ