“የተቃጣብንን ዘርፈ ብዙ ጥቃት መመከት የቻልነው በአንድነት ስለተነሳን ነው”

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የተቃጣብንን ዘርፈ ብዙ ጥቃት መመከት የቻልነው በአንድነት ስለተነሳን ነው” አሉ።
ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና ባለሃብቶች፣ የጥበብ ባለሙያዎችና ዲያስፖራዎች ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት እና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ሲያደርግ ነው።
“ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ የለም” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የድጋፍ ፕሮግራም ላይ የቴክኒክ ሙያ ሥልጠናና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) የተሰበሰበውን 23 ሚሊዮን 242 ሺህ 290 ብር የሚገመት ድጋፍ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ አስረክበዋል።
አንጋፋዋ አርቲስት ሀመልማል አባተ አንድ ሚሊዮን፣ የአሌክሳንድሪያ ሆቴል ባለቤት ዮሐንስ ደርሶ 5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በቀለ አረና የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ከንቲባዋ በአሸባሪው ቡድን የወደሙ አካባቢዎችንና ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋምና በራስ አቅም ብልፅግናና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ትብብራችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
እስከአሁን በከተማ ደረጃ በ3ኛው ዙር ብቻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለአገር መከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በወራሪው ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ማቋቋሚያ የሚውል ሃብት መሰብሰብ መቻሉን ከንቲባዋ አስታውቀዋል።