የተቋማቱ የጋራ ትብብር ማዕከል ተከፈተ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እና ዓለም ዐቀፉ የክትባት ኢንስቲትዩት የጋራ የትብብር ማዕከል ተከፈተ።

ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ከአንድ ዓመት በፊት በመፈራረም የተለያዩ ሥራዎችን ስሰሩ ቆይተዋል።

አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ሻሉ ዳባ (ዶ/ር) አርማወር የምርምር ኢኒስቲትዩት በመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከምርምር ሥራዎች ጎን ለጎን ክትባትን በማበልፀግና በፋርማሲቲካል በኩል የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተው ከዓለም ዐቀፍ ክትባት ኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ መስራቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

በክትባት ተደራሽነት፣ በክትባት ማበልጸግ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም አቅምን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ውጤት እንደሚያመጣም ተናግረዋል።

የዓለም ዐቀፍ ክትባት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጆርም ኪም (ዶ/ር) የሁለቱ ተቋማት አጋርነት በኢትዮጵያ በክትባት ተደራሽነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግርና በበርካታ መስኮቶች ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጄ ደጉማ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተው የኮርያ ሆስፒታል በኢትዮጵያ እየሰጠ ስላለው የጤና አገልግሎት አመስግነዋል።

ዓለም ዐቀፍ ወይም ኢንተርናሽናል ክትባት ኢኒስቲትዩት እና አርማወር በጋራ መስራታቸው በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውን አንስተዋል።

ኢኒስቲትዩቱ ከክትባት ተደራሽነት አንጻር በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሁለቱ ተቋማት አጋርነት ክትባት በማበልጸግ፣ በአቅም ግንባታ በቴክኖሎጂ ሽግግር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ክትባት ኢኒስቲትዩት ዋና መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ያደረገ እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አነሳሽነት ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግሥታዊ ድርጅት ነው።

ክትባቶችን ለዓለም በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ ላይ ያለመው ተቋሙ የኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ስዊድን፣ ሕንድ እና ፊንላንድ ጨምሮ በ36 ሀገራት የተመሰረተ ነው፡፡

ድርጅቱ በመላው ዓለም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመግታት የክትባት ተደራሽነት ላይ ይሰራል።

ተቋሙ ከአርማወር ጋር በጀመረው ፕሮጀክትም በሻሸመኔ ከተማና ቀበሌዎች የኮሌራ ክትባት መስጠት ጀምሯል።

በመስከረም ቸርነት