የተቋማት ኃላፊዎችና ሰራተኞች በምስራቅ ሸዋ ዞን የፓፓያ ልማትን ጎበኙ

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ በክላስተር የለማ የፓፓያ ምርት ጎበኙ።

በጉብኝቱ የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ በዞኑ ለፓፓያ እና አቮካዶ ክላስተር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችም በክላስተር በመደራጀት ከፍተኛ ምርት በማግኘት ህይወታቸውን በመለወጥ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በዞኑ በ1 ሺሕ 690 ሄክታር መሬት ላይ የፓፓያ ክላስተር ለምቶ በመመረት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

በቀጣይም የፓፓያ እና አቮካዶ ምርትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በክላስተር ፓፓያ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ አምራች እየሆኑና በኑሯቸውም ላይ ለውጥ ማምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ በሚያገኙት ገቢ ሀብት እያፈሩ ስለመሆኑም ተናግረዋል።