የተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ግጭቶች እንዲቀንስ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ትምህርት ተደራሽነት ድጋፍ አደርጋለሁ አለ

ጥር 28/2014 (ዋልታ) –የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ በአፍሪካ ግጭቶች እንዲቀንሱ፣ ለወጣት አፍሪካዊያን የሥራ እድል እንዲፈጠርና የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ መንግሥታቱ ለአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፁ።
በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በበይነመረብ ንግግር ያደረጉት ዋና ፀሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ አፍሪካን እየፈተኗት ካሉ ጉዳዮች መካከል ዋናዎቹ የአስተዳደር፣ የሰላምና ፀጥታ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም አኅጉሪቱ የሰብኣዊ መብት ጥሰት፣ የሰብኣዊ ድጋፍ አለመዳረስ፣ ሽብርተኝነት፣ የፀጥታ እና የኮቪድ ክትባት ችግሮችን ለመፍታት እየተስተዋለባት እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡
በአፍሪካ አኅጉር እምርታ እያሳየባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል የግብርና ምርቶች ማሳደግ፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ የሚደረገው ጥረት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር፣ የግል ዘርፍ መነቃቃትና ሰላሟ የተረጋገጠ አኅጉር ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችንም አድንቀዋል።
በተለይም ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት እድገት መጨመር የሚበረታታ ነው ያሉት ዋና ፀሀፊው አጀንዳ 2063 የኅብረቱ አባል አገራት የጋራ ትልምና ዓላማ የያዘ በመሆኑ ለውጤታማነቱ በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
ይህ ብቻ አይበቃም አባል አገራቱ የኢኮኖሚ ምንጭ ማሳደግ አለባቸው፤ ግጭቶችን መቀነስና ወጣት አፍሪካዊያን የሥራ እድል እንዲፈጠርና የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ የኅብረቱ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
እነዚህ ውጥኖች እንዲሳኩ የተባበሩት መንግሥታት ለአፍሪካ ኅብረት ድጋፍን አጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ተናግረዋል፡፡
በደረሰ አማረ
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!